ካንድ አመት በኋላ ጌታየ ሀብቱ ሞተብንና እጅግ አዘንን፡፡ ትልቅ ለቅሶ አለቀስን እሱ ሳይሞት ጠርቶ ይኸው እኔ እሞታለሁ
እግዚያብሔር ይጠብቃችሁ ይባርካችሁና አንተም ለልጆቼ አባት ሁናቸው አለኝ፡፡ አንድ በሬና አንድ በቅሎም ሰጠኝ፡፡
ለሚስቴም ሁለት ላሞች ከነልጆቿ ሰጣት፡፡ ስለነፍሴ ፀልዩ ብሎን በእግዚያብሔር ሰላም ሞተ፡፡ እርሱ በተባረከች ነፍሱ
አረፈና በትልቅ ክብርም ቀበርነው፡፡ የበኩር ልጁ ወልደ ሚካኤል የተባለውም እንደ አባቱ ወደደኝ፡፡ ምክሬንም ይሰማ
ነበር፡፡ ስሟ ወለተ ጴጥሮስ ፋንታየ የተባለች ሚስትም ነበረችው፡፡ እርሷን የከበረች የክቡራን ወገኖች ነበረች፡፡ መልካም
ምግባርና ሰው ወዳጅ ትህትና የሞላች ናት፡፡ እናት ልጅዋን እንደምትወድ ትወደን ነበር፡፡ ሁለቱ የጌታየ ሀብቱ ልጆች
ተሰማና ምትኩ አድገው ዳዊት ማንበብ አወቁ፡፡ ምትኩ ግን እንደገና ሰዋሰው መፃህፍት አወቀና በፅኑ ፍቅርና እውቀት ከእኔ
ጋር አንድነት ያለው ሆነ፡፡ እርሱ ሚስጥሬን ሁሉ ያውቃል፡፡ ለእርሱ የሸሸኩት የለም፡፡ ብዙ ጊዜ ከለመነኝ በኋላ ስለፍቅር
ብየ ይህችን ትንሽ መፅሃፍ ፃፍኩ፡፡