ልጄም አድጎ ያማረ ጎበዝ ሆነ፡፡ ሃያ ዓመትም በሆነ ጊዜ እርሱ ባለማወቅ ወደ ምንኩስና እናዳዘነበለ አወቅሁ፡፡
"ይህ ስራ ፈጣሪ ለኛ የሰራልንን ሥርዓት ያፈርሳልና አይገባም" ብየ ብዙ ተቆጣሁት፡፡ "ነገር ግን በተፈጥሯችን ስርዓት ሚስት
አግብተህ ኑር" አልኩት፡፡
"እሺ ሚስት ስጠኝ" አለኝ፡፡
ላምጌ ከተባለው አገር መድሃኒት የተባለች የአርብቶ አደሮችን አለቃ ያማረች ልጅ ፈልጌ አገኝሁ፡፡ ልጄም በእርሷ ተደሰተ፡፡
አባቷም አስራ አምስት ከብቶችና ልብሶችም ሰጣት፡፡ ለልጄም ሚስት ሆነችው አብረውም በፍቅር ነበሩ ፡፡ ከሁለት አመትም
በኋላ ወንድ ልጅ ወለደች፡፡ ደስታየ አልኩት፡፡ መልሳም ሴት ልጅ ወለደች ዋጋየ አልኳት፡፡ ከመልካም ሁሉ ያጠገበኝ
እግዚያብሔርን አመሰገንኩት፡፡ እኔም ለሰዎች ክርስቲያን እመስላቸው ነበር፡፡ ነገር ግን በልቤ እርሱ እንዳስታወቀኝ የሁሉ
ፈጣሪና የሁሉ ጠባቂ በሆነ በእግዚያብሔር ካልሆነ በስተቀር በማንም አላምንም፡፡ አማኝ ሳልሆን አማኝ እመስላለሁ፡፡
በእግዚያብሔር ዘንድ ይህ ያስቀጣኝ ይሆን? ብየ አሰብኩ፡፡ ሰዎችን እንዲህ አታልላቸዋለሁ፡፡ ሰዎችን ማታለል ይገባልን?
አልኩ፡፡ እውነቱን ብነግራቸው ለሰዎች ትልቅ ጥፋት ካልሆነ በስተቀር ሃሳቤን መግለፄ ጥቅም የለውም፡፡ሊሰድቡኝና
ሊያባርሩኝ ካልሆነ በስተቀር አይሰሙኝም፡፡ ስለዚህ እነርሱን መስየ ከሰው ጋር እኖራለሁ አልኩ፡፡ እርሱ እንዳስታወቀኝ
በእግዚያብሔር ዘንድ ኖርኩ፡፡ ከኔ በኋላ የሚመጡ እንዲያውቁ ግን እስክሞት ድረስ በእኔ ዘንድ ሸሽጌ የምይዘውን ይህን
መፅሃፍ በተማሪየ ገፋፊነት ልፅፍ ወደድኩ፡፡ ከሞቴ በኋላ አዋቂና መርማሪ ሰው ቢገኝ ግን በሃሳቤ ላይ ሃሳቡን
እንዲጨምርበት እለምነዋለሁ፡፡ ይኸው እኔ ከዚህ በፊት ያልተመረመረውን መመርመር ጀመርኩ፡፡ የሃገራችን ሰዎች
በእግዚያብሔር ረድኤት አዋቂዎች እንዲሆኑ፣ እውነትንም ወደማወቅ እነዲደርሱ፣ ሐሰትን እንዳይፈልጓትና አመፃንም ተስፋ
አድርገው ዝም ብለው ከከንቱ ወደ ከንቱ እንዳይሄድ እውነትን እንዲያውቁና ወንድሞቻቸውን እንዲወዱ፣ እንግዲህ እስከ
አሁን እንደሚደርጉት በከንቱ በሃይማኖታቸው እንዳይጣሉ እኔ የጀመርኩትን አንተ ጨርሰው ይህንን ያወቀና ከዚህም
የተሻለ እሚያውቅ ቢገኝ ያስተምረውና ይፃፈው፡፡ እግዚያብሔር እንደ ልቡ ይስጠው፡፡ ፈቃዱን ሁሉ ይፈፅምለት፡፡ እኔ
እንዳጠገበኝ ሥፍር በሌለው መልካምም ያጥግበው፡፡ እኔን እስከ ዛሬ ብፁዕ አድርጎ እንዳስደሰተኝ በዚህ ምድር ብፁዕ
አድርጎ ያስደስተው፡፡ በዚህ መፅሃፌ ከኔ በላይ እሚሳደብና እንዲያምርለት የሚፈልግ ግን እግዚያብሔር እንደ ምግባሩ
ይስጡ አሜን፡፡