እግዚያብሔር የገዛ ህዝቡን እንዲያስቷቸው ስለምን ዋሾ ሰዎችን ይተዋል ብዮ አሰብኩ፡፡ እግዚያብሔር ግን ለሁሉም
ለእያንዳንዱ እውነትንና ሐሰትን እንዲያውቅ ልቦና ሰጥቶናል፡፡ እውነት ወይም ሐሰት እንደፈቃዱ የሚመርጥበት
መምረጫም ሰጠው፡፡ እውነትን ብንወድ ለፍጥረት ሁሉ አስፈላጊና ተገቢ የሆነውን እርሱም እንድናይበት እግዚያብሔር
በሰጠን ልቦናችን ውስጥ እንፈልጋት፡፡ ሰው ሁሉ ዋሾ ነውና እውነትንም በሰዎች ትምህርት አታገኟትም፡፡ ከእውነት ይልቅ
ሐሰትን ብንመርጥ ስለዚህ እኛ በስህተታችን እንጠፋለን እንጂ ለፍጥረት ሁሉ የተሰራው የፈጣሪ ስርዓትና ሕግ አይጠፋም፡፡
እግዚያብሔር ማንንም በሠራው ሥራ ይጠብቀዋል፡፡ ከሰው ስራ ግን የእግዚያብሔር ስራ ይፀናል፡፡ የሰው ስራ ሊያጠፋው
አይችልም ስለዚህም ከጋብቻ ይልቅ ምንኩስናን ይበልጣል ብለው የሚያምኑ እነርሱ በፈጣሪ ስራ ፅናት ወደ ጋብቻ
ይሳባሉ፡፡ ፆም ነፍስ እንደሚያፀድቅ የሚያምኑ እነርሱ ደግሞ እረሃብ በበዛባቸው ጊዜ ይበላሉ፡፡ ገንዘቡን የተወ ፍፁም
እንዲሆን የሚያምኑ በገንዘብ ለሚያገኙት ጥቅም ወደ ገንዘብ መፈለግ ይሳባሉ፡፡ ብዙዎች የሀገራችን መነኩሴዎችም
እንደሚደርጉት ከተውት በኋላ እንደገና ይፈልጉታል፡፡ እንደዚሁ ዋሾዎች ሁላቸው የተፈጥሮን ሥራ ሊያፈርሱ ይፈልጋሉ፡፡
ነገር ግን ደካማነታቸውን ያሳያሉ እንጂ አይችሉም፡፡ ፈጣሪም ይስቅባቸዋል፡፡ የፍጥረት ጌታም በላያቸው ይሳለቅባቸዋል፡፡
እግዚያብሔር የእግዚያብሔርን ፍርድ ማድረግ ያውቃልና ሃጥአንም በእጁ ሥራ ወጥመድ ተጠመደ፡፡ ስለዚህም የጋብቻን
ሥርዓት የሚያስነውር መነኩሴ በክፉ በሽታና ፍጥረቱ ባልሆነ በሌላ የሴት አበሳ በዝሙት ተፅኖ ይጠመዳል፡፡ ገንዘባቸውን
የሚንቁ ገንዘብ እንዲያገኙ በሀብታሞችና በነገስታት ዘንድ ግብዞች ይሆናሉ፡፡ ለእግዚያብሔር ብለው ዘመዶቻቸውንም
በሽምግልናቸው በችግራቸው እረዳት ባጡ ጊዜ የተው በነሱ ሽምግልና ጊዜ ሰውና እግዚያብሔርን ወደ ማማት መሳደብ
ይደርሳሉ፡፡ እንደዚሁም የፈጣሪን ሥርዓት የሚያፈርሱ ሁሉ በእጃቸው በሰሩት ወጥመድ ይወድቃሉ፡፡ እንደገናም
10
እግዚያብሔር ክፋትን ስህተትን በሰው መካከል ይተዋል፡፡ ነፍሶቻችን በዚህ ዓለም የእግዚያብሔር ጥበብ የፈጠረውን
የፈተና ቀን ይኖራሉ፡፡
ጠቢቡ ሰለሞን
"እግዚያብሔር ፃድቃንን ፈተናቸው፡፡ ወርቅ በእሳት እንደሚፈተን ይፈትናቸዋል፡፡ ለእርሱ የተዘጋጁ ሆነውም
አግኝቷቸዋልና፡፡ እንደተወደደ ዕጣን መአዛም ይቀበላቸዋል" ይላል፡፡
ከሞታችን በኋላም ቢሆን ወደፈጣሪያችን በገባን ጊዜ እግዚያብሔር በእውነትና በትልቅ በጥበብ ከሠራው ሁሉ እውነትና ቅን
የሆነውን መንገድ ሁሉ እንለያለን፡፡ ነፍሳችንም ከስጋዊ ሞታችን በኋላ እንደምትድን ይታወቃል፡፡ በዚህ ዓለም ውዴታችን
አይፈፀምምና የሌላቸው ይፈልጋሉ ያላቸው ባላቸው ላይ እንደገና ሊጨምሩ ይፈልጋሉ፡፡ ሰው በዚህ ዓለም ያለው ሁሉ
እንኳን ቢኖረው እንደገና ይወለዳል እንጅ አይጠግብም፡፡ ይህም የፍጥረታችን ጠባይ ለሚመጣው ንብረት እንጅ ለዚህ
ዓለም ንብረት ብቻ እንዳልተፈጠርን ያመለክታል፡፡ በዚያውም የፈጣሪያቸውን ፈቃድ የፈፀሙ ነፍሳት ፍፁም ይጠግባሉ
እንጅ ከእንግዲህ ሌላ አይወዱም፡፡ አለዚያ ግን የሰው ፍጥረት አስፈላጊውን ሁሉ አላገኝምና ጎዶሎ በሆነ ነበር፡፡ እንደገናም
ነፍሳችን እግዚያብሔርን ማሠብ ትችላለችና በሃሳቧም ታየዋለች፡፡ እንደገናም ለዘላለም መኖር ማሰብ ትችላለች፡፡
እግዚያብሔርም ይህን ማሰብ በከንቱ አልሰጣትም፡፡ ነገር ግን እንደሰጣት ልታስብና እንድታገኝም ሰጣት፡፡ ደግሞ በዚህ
ዓለም ፅድቅ ሁሉ አይፈፀምም፡፡ ክፉ ሰዎች ከዚህ ዓለም መልካም ይጠግባሉ፡፡ ደጋጎች ይራባሉ፡፡ እሚደሰት ክፉ አለ፣
እሚያዝን ደግ አለ፣ እሚደሰት አመፀኛ አለ፣ እሚያለቅስ ፃድቅም አለ፣ ስለዚህም ከሞታችን በኋላ ለሁሉ እንደየምግባሩ
እሚከፍለው ሌላ ኑሮና ፍፁም ፅድቅ ያስፈልጋል፡፡ በብርሀን ልቦናችን ተገለፀላቸው፡፡ የፈጣሪን ፈቃድ የፈፀሙና
በተፈጥሯቸውም ፀባያዊ ህጉን የጠበቁ ዋጋቸው ይከፈላቸዋል፡፡ የተፈጥሮን ህግ ከመረመርን የተረጋገጠ መሆኑን ልቦናችን
በግልፅ ይነግረናል፡፡ ነገር ግን ሰዎች ሊመረምሩ አልፈለጉምና የፈጣሪያቸውን ፈቃድ በእውነት ከመፈለግ የሰዎችን ቃል
ማመን መረጡ፡፡