በ 1635 ዓ/ም በህዝብ ሃጢያት እና ፍቅረቢስነት ፍቅር ማጣት በኢትዮጵያ ሁሉ ትልቅ እረሃብ ብርቱ መቅሰፍት ሆነ፡፡ ንጉስ
ሱስንዮስና የአቦነ አልፎንዝን ሃይማኖት የተቀበሉ ሃይማኖታቸውን ያልተቀበሉ ወንድሞቻቸውን መጀመሪያ ገደሉ፣ አባረሩ፡፡
የተሰደዱትም በኋላ ከጠላቶቻቸው ብዙዎቹን ገደሉና አፀፋ መለሱ፡፡ በኋላቸውም ሆነ በፊታቸው የእግዚያብሔር ፍርሀት
እንደሌለና የሰላምንም መንገድ እንዳላወቋት በግልፅ ታወቀ፡፡ በከንቱም ክርስቲያኖች ተባሉ እየሱስ ክርስቶስ ግን ከሁሉ
አስቀድሞና ከሁሉ በላይ ክርስቲያኖችን እርስ በርሳቸው እንዲፋቀሩ አዟቸዋል፡፡ ይህ ፍቅር የተባለው ግን ክርስቲያኖች
በተባሉት መካከል ፈፅሞ ጠፋ፡፡ ሁሉ ወንድሞቻቸውን ይበድላሉ፡፡ እርስ በርሳቸው እንደ እህል አበላል ይዋዋጣሉ፡፡
ፋሲለደስም በመልካም ምክርና ጥበብ መንገስ ጀመረ፡፡ ነገር ግን ደም በማፍሰስ አመፀኛ ንጉስ ሆኖ በክፋቱ ፀና እንጅ
መልካሙን አልመረጠም፡፡ መንግስቱን በመልካም ጥበብ ያበጁለትን መልካም ቤቶችና ምሽጎች የሰሩለትን ፈረንጆች
ጠላቸውና አባረራቸው፡፡ በመልካም ፋንታ ክፉ መለሰላቸው፡፡ ይህም ፋሲለደስ በሁሉም ክፉ አድራጊ ሆነ፡፡ ሰዎችንም
አለፍቅር አለፍርድ ገደለ፡፡ ዝሙትንም አበዛ፡፡ ሴቶችን ዝሙቱን ከፈፀመባቸው በኋላ ገደላቸው፡፡ አመፅ የሚሰሩ ሰራዊቶችን
ሁሉ እየሰደደ የድሆችን ቤትና አገሮች አስወረረ፡፡ እግዚያብሔርም ለክፉዎች ሕዝቦች ክፉ ንጉስ ሰጣቸው፡፡ በንጉሱና
በሕዝቡ ሀጢያትም ረሃብና መቅሰፍት መጣ፡፡ ከረሃብ በኋላ ቸነፈር ሆነና ብዙዎቹ ሞቱ፡፡ ሌሎችም ለመዳን ያልሆነ ፍርሃት
ፈሩ፡፡ በእብደታቸው ፀንተዋልና ግማሾቹ አቡነ አልፎንዝን ስላባረራችሁት የእግዚያብሔር መቅሰፍት በላያችሁ መጣ አሉ፡፡
ግማሾቹ ደግሞ የቀድሞዋን ሃይማኖት ስለከዳችሁ ቤተክርስቲያን ስላረከሳችሁ ይህ መቅሰፍት መጣ እየተባባሉ እርስ
በረሳቸው ተጣልተው ተለያዩ፡፡ እግዚያብሔር ለሁሉ ፍጥረት የሰራውን እውነተኛውን ሥራ ፍቅረ-ቢስ የሰው ስርዓት
ሰላፈረሱና ስለተላላፍ መቅሰፍት እንደመጣባቸው አላወቁም፡፡ ሃይማኖት እንዲህ ነው ወይም እንዲያ ነው የሚለውን
ስለሰው ሕግጋት ሲሉ ዋና ዋና ሕግጋትን ሻሩ፡፡
ኢሳያስም ወንጌል ስለነርሱ ተናገረ፡
"እነዚህ ህዝቦች በአፋቸው ያከብሩኛል፡፡ በልባቸው ግን ከእኔ እጅግ ይርቃሉ፡፡ ሰውን ስርዓትና ትምህርት እያስተማሩም
በከንቱ አመለኩኝ" አለ፡፡
19
ደግሞ ዩሐንስም፡
"በብርሃን አለሁ እያለ ወንድሙን የሚጠላ ዋሾ ነውና እስከዛሬ በጨለማ ይኖራል፡፡ወንድሙን የሚወድ ግን በብርሃን
ይኖራል፡፡ በእርሱ ዘንድ እንቅፋት የለም፡፡ ወንድሙን የሚጠላ ደግሞ አይኖቹን ጨለማ አሳውሮታልና በጨለማ
ይመላለሳል፡፡ ወዴት እንደሚሄድ አያውቅም፡፡" አለ፡፡
ይህም ትንቢት በሀገራችን ሰዎች ላይ ተፈፀመ፡፡ የሚሄዱበትን አያውቁምና ስለሃይማኖታቸው ይጣላሉ፡፡ የሚያምኑትን
አያውቁምና በጨለማ ይኖራሉ፡፡ እኛ ግን በረሃብ ጊዜ ወርቃችን ካለቀ በኋላ እግዚያብሔር ምስጋና ይድረሰው ከብቶቻችንና
ልብሶቻችንን ሸጠን በላንና የተራቡትን፣ የታመሙትን አበላን እንጅ እንደ ሌሎች አልተራብንም፡፡ አራት አመት ሆነው
ረሃብን ቸነፈር አልተራብንም አልታመምንም፡፡ በክፉ ቀኖች አያፍሩም በረሃብ ጊዜም ይጠግባሉ የተባለው በእኛ ላይ
ተፈፀመ፡፡ ቁጥር የሌለው መልካምም ለኛ ስላደረገልን እግዚያብሔርን አመሰገንነው፡፡